ስማርት ፎንን በመጠቀም በሰውነት ውስጥ የሚገኘውን ጭንቀት አምጪ ሆርሞን መጠን ማወቅ የሚቻልበት ዘዴ ምርምር ይፋ ሆነ


 

ሰዎች ዘመናዊ ተንቀሳቃሽ ስልኮችን (ስማርት ፎንን) በመጠቀም በሰውነታቸው ውስጥ የሚገኘውን የድብርት (ጭንቀት) አምጭ ሆርሞን መጠን በትክክል ማወቅ የሚያስችላቸው የምርምር ውጤት ይፋ መደረጉን ከሮይተርስ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል::

“ዘ ኢንዶ ክራይን ሶሳይቲ ኤንድ ኢንተርናሽናል ሶሳይቲ ኦፍ ኢንዶክሪኖሎጂ” የተባሉት ማህበራት በጋራ ሰሞኑን ቺካጐ ውስጥ ባዘጋጁት ጉባኤ ላይ ነበር የምርምር ውጤቱ ይፋ የተደረገው::

ታዲያ ይህ ቀላል ቱቦን፣ ሶፍትዌርን፣ ናሙና አንባቢ ቁስ እና የምራቅ ናሙናን ብቻ በመጠቀም በሰውነት ውስጥ ከሚገኙት የድብርት (ጭንቀት) አምጭ ሆርሞኖች መካከል የሚመደበውን የኮርቲሶል መጠን በትክክል ማወቅ ይችላሉ::

“እኛ በምርምር ያገኘነው ዘዴ ማንኛውም ሰው ዘመናዊ ስልኩን /ስማርት ፎንን/ በመጠቀም በምራቅ ውስጥ የሚገኘውን የኮርቲሶል ሆርሞን መጠን በቀላሉ፣ በፍጥነት እና በአነስተኛ ዋጋ እንዲያውቅ የሚያስችል ነው ብለዋል ዶ/ር ጆየል ህሬንክራዝ የተባሉት የግኝቱ ዋና ተመራማሪ::

 

Smartphones
Smartphones

በአሁኑ ወቅት በአሜሪካ የሚገኙ ቤተ ሙከራዎች በሰውነት ውስጥ ያለውን የኮርቲሶል ሆርሞን መጠን ለማወቅ ለሚፈልግ ሰው እስከ 50 ዶላር ያስከፍላሉ:: ውጤቱም ቢሆን የሚታወቀው የአንድ ሳምንት ያህል ጊዜን ወስዶ ነው::

በአንፃሩ ዘመናዊ ስልኮችን /ስማርት ፎንን/ በመጠቀም ተመሳሳይ ተግባር ለመፈፀም ግን ከአምስት ዶላር ያልበለጠ ገንዘብ እና ከ10 ደቂቃ ያልበለጠ ጊዜ ብቻ በቂ መሆናቸውንም ዋና ተመራማሪ ዶ/ር ጀየል ገልፀዋል:: በምርምር ውጤቱ መሰረት ዘመናዊ ስልኮችን በመጠቀም በሰውነት ውስጥ ያለውን የኮርቲሶል መጠን ለማወቅ የሚያስፈልጉ ነገሮችም ተዘርዝረዋል:: ከስልኩ ቀጥሎ ናሙና አንባቢ /ሪደር/ ደግሞ ዋናው ነው::

ይህ ናሙና አንባቢ ከኬዝ፣ ከብርሃን ቱቦ እና ከሌንስ ተውጣጥቶ የተሰራ ነው:: ለሀይል ምንጭ የሚሆን ምንም አይነት ባትሪ የለውም /አያስፈልገውም/:: በቀላሉ የማይሰበር ከመሆኑም ባሻገር ተደጋግሞ ሊጠቀሙበት የሚችል ነው:: የምራቅ ናሙና መውሰጃ ስትሮው እና በናሙና አንባቢው ውስጥ የምትሰካ ናሙና ተቀባይ /ስትሪፕ/ ደግሞ ሌሎቹ አስፈላጊ ነገሮች ናቸው::

አንድ ሰው ምርመራውን ለማካሄድ በመጀመሪያ ምራቅን በቀላሉ መሰብሰብ የሚችለውን ስትሮው በምላሱ ስር ያስገባል:: ይህ ስትሮው ምራቅን ሰብስቦ በቀላሉ በካፒላሪ አክሽን /ውስጥ ለውስጥ በማስረግ/ ወደ ናሙና መቀበያው ስትሪፕ ማለትም በናሙና አንባቢው /ሪደሩ/ ውስጥ ወደ ተሰካችው ያስተላልፋል::

ከዚህ በኋላ ናሙና አንባቢው በውስጡ ካሉት ሌንስ እና ብርሃን አስተላላፊ ቱቦ ጋር በመቀናጀት ከዘመናዊ ተንቀሳቃሽ ስልኩ በሚረጨው ብርሃን እና በካሜራው አማካኝነት መረጃውን ያስተላልፋል:: ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላም ለዚሁ ተብሎ በተዘጋጀው ሶፍትዌር አማካኝነት በዘመናዊ ስልኩ ካሜራ የተወሰደው ምስል ይተረጐምና በናሙናው ውስጥ ያለው ኮርቲሶል መጠን በቁጥር ይተረጐማል::

“የኮርቲሶል መጠን መለኪያው ዘዴ ማለትም የዘመናዊ ስልኩ እና ናሙና አንባቢው አሰራር እንደ ፎቶ ስቱዲዮ ነው:: አስቸጋሪው እና ውስብስቡ ሂደት በቀላሉ ወደ ስትሪፕ ኬምስትሪ ተለውጦ ወደ ዘመናዊ ስልኩ ሶፍትዌር መድረስ ነው::

ስለሆነም ማንኛውም ሰው ሀይል የተሞላ (ቻርጅ) ዘመናዊ ስልክ እና የናሙና መውሰጃ /ኪት/ ካለው በቀላሉ ትክክለኛውን በሰውነት ውስጥ የሚገኝ የኮርቲሶል መጠን ማወቅ እንደሚችል የገለፁት ደግሞ ዶ/ር ራንዳል ፓልሰን የተባሉት የኦፕቲካል ኢንጅነር እና የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ናቸው::

ዶ/ር ጆየል እና ሌሎች የምርምር ቡድኑ አባላት በአሁኑ ወቅት ዘመናዊ ስልኮችን በመጠቀም በኮርቲሶል ሆርሞን መጠን መብዛት ወይም ማነስ ምክንያት ችግር ያለባቸውን ሰዎች በመለየት እርዳታ የሚያደርጉ የጤና አገልግሎት ተቋማትን በማፈላለግ ላይ ናቸው:: ይህም በሰዎች ውስጥ ያለው የኮርቲሶል መጠን በቀላሉ ለመቆጣጠር ያግዛል::

ተመራማሪዎች ወደ ፊትም ሁሉም ሰው በሰውነቱ ውስጥ የሚገኘውን የኮርቲሶል መጠን በቀላሉ በፈለገ ጊዜ ማወቅ እንዲችል ለዚሁ የሚያገለግሉ ቁሳቁሶች ዋጋ በዝቅተኛ ዋጋ የሚቀርቡበትን እና በማንኛውም ተንቀሳቃሽ ስልክ መጠቀም እንዲችል የማድረግ ሀሳብ አላቸው::

ዘመናዊ የህክምና ቁሳቁሶች የተሟሉላቸው የጤና ተቋማት ለሌሏቸው እና ይህንኑ የማድረግ አቅም ለማይኖራቸው ታዳጊ አገራት ጥሩ መፍትሄ እንደሆነም ታምኖበታል:: ለዚህም ይመስላል የታይላንድ የጤና ሚኒስቴር ዘመናዊ ስልኮችን በመጠቀም በሰዎች ውስጥ ያለውን የኮርቲሶል መጠን ማወቂያ ዘዴ ከዚህ አመት መጨረሻ አካባቢ ጀምሮ በአገሪቱ ለማስተዋወቅ ያቀደው::

Admin

Advertisements

Comment

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s